ተቋሙ ለሁለት ቀናት በሐረር ከተማ ሲያከናውን የነበረውን የቅርንጫፎችና የዋናው መሥሪያ ቤት የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩን በዛሬው ዕለት አጠናቋል።
በግምገማ መድረኩ በድሬዳዋ፤ በሐረር፤በጅግጅጋ እና በሐረማያ ያሉት ቅርንጫፎች የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ከዚህም በተጨማሪ የኦፕሬሸንና የፋይናንስ ዘርፍ እንዲሁም የዋስትና ፈንድ ብድር አመላለስና ነባር የብድር ደንበኞችን ከቁጠባ ጋር በማስተሳሰር ረገድ የተሰሩ ሥራዎች አፈጻጸምም በመድረኩ ቀርቧል።
መድረኩን የመሩት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ም/ዋና ሥራአስፈጻሚና የኤም.አይ.ኤስ ዳይሬክተር አቶ ፋሲል ጌታቸው በቁጠባ አሰባሰብ ረገድ የታዩ መልካም አፈጻጻሞችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በጠቆሙበት ንግግራቸው የወጣቶችና ሴቶችን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚነት በማሳደግና የደንበኞች ዕርካታን በመጨመር ረገድ አፅንኦት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ቁጠባ ላይ የተፈጠረውን ትስስር በወጥነት መከታተል እንደሚያስፈልግ ያከሉት አቶ ፋሲል ከብድር ስርጭት ባሻገር ቁጠባ መሠረታዊ ነገር በመሆኑ ቁጠባ አሰባሰብ ላይ ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አሁን ላይ የተቋሙ ደንበኞች እጅ ያለ የብድር መጠን ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑንና ከ720 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል እንዳለው እንዲሁም በብድር ስርጭት ረገድከ727ሚሊየን ብር በላይ ከ3ሺ በላይ ለሆኑ ሰዎች በመስጠት በቅደም ተከተል በብር 80 በመቶ በሰው ደግሞ 91 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል። የአደጋ ስጋት ላይ ያለ ብድርን /ፓር/ ምጣኔን ደግሞ ከ91 ቀን በላይ ያለውንም ወደ 0.78 እንዲቀንስ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
አቶ ፋሲል ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ዕመርታ እያሳየ መሆኑን አንስተው ይህ የሆነው በጠቅላላ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ቅንጅታዊ አሰራርና ተቀራርቦ እንደ ቤተሰብ በቡድን ስሜት በመሥራት በመሆኑ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።










Leave a Reply