የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የዎሽ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ
ወጣት ፍሬዘር አበበ ቁርጠኝነትን የተላበሰች፣ ወጣትነቷ የብርታትዋ የማዕዘን ድንጋይ የሆነላት፣ ያሰበችውን ከግብ ለማድረስ ትጋትና ተስፋን አሰናስላ የምትጓዝ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ደንበኛ ናት፡፡ በዚህም ጥረቷ በድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ደንበኝነት ከተቋሙ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ችላለች፡፡ የህይወቷን የአኗኗር ዘይቤ የቀየረው፣ በተለየ ሁኔታ ለውጥ ቀያሪው ያገኘችው አንዱና ዋነኛው የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ሳኒቴሽንና ሃይጅን /ዎሽ/ የብድር አገልግሎት ነው፡፡
ይህን አገልግሎት ከማግኘታቸው በፊት ፍሬዘር እና ቤተሰቧ ከንፁህ መጸዳጃ እና ተያያዥ የዎሽ አገልግሎቶች አንጻር ተግዳሮት ይገጥማቸው የነበረ ሲሆን ይህን የዎሽ የብድር አገልግሎት ማግኘታቸው ግን ችግሩን ከስሩ ፈቶላቸው ዛሬ ላይ የደስታን ብርሃን ማየት ጀምረዋል፡፡
ደንበኛዋ ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ባገኘችው የዎሽ ብድር አገልግሎት መፀዳጃ ቤት፣ ሻወር ቤትና ሴፍቲ ታንከር ማሰራት የቻለች ሲሆን ይህም እሷና ቤተሰቧ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖራቸው እንዳስቻላቸውና እንደ አጠቃላይ የዎሽ ብድር አገልግሎት በብዙ እንደጠቀማቸው ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች፡፡
የዎሽ ብድር አገልግሎት በድሬ ማይክሮ ፋይናንስ መጀመሩ ለማኅበረሰቡ አካባቢው ንፁህ እንዲሆንና ጤናማ ህይወት እንዲኖረው በማስቻል ረገድ አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ያመላከተችው ወጣት ፍሬዘር ይህ አገልግሎት ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንዳለው በመጥቀስ ማኅበረሰቡ የዎሽ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ከእሷ ተሞክሮ በመነሳት መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡
የፍሬዘር ታሪክ የፋይናንስ አካታችነት ከሴቶች ተጠቃሚነትና ማብቃት ጋር፣ ቤተሰቦችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከማድረግና ማኅብረሰብን ከመድረስ አንጻር ብዙ ስራ መስራት እንደሚቻል አመላካች ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማኅበረሰባዊ ፋይዳ ካላቸውና አዎንታዊ ሚና ከሚጫወቱ ፕሮግራሞች ጋር አቀናጅቶ መጓዝ ከተቻለ ዘላቂ የሆነ ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡




Leave a Reply