ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከተለያዩ ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር የተቋሙን ገጽታ በሚገነቡ ብሎም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡና ከምንም በላይ የማኅበረሰቡን የፋይናንስ አካታችነትና ተደራሽነት ዕውን በማድረግ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚያስችሉ አግባቦች ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም አግባብ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ጋር በጋራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ስለ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ታሪካዊ ዳራ፣ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ብሎም አጠቃላይ እንቅስቃሴና እያበረከታቸው ስላሉ ማኅበረሰባዊ ፋይዳዎችና በሌሎችም ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር በማስፈለጉ 40 ለሚደርሱ የማኀበሩ አመራርና አባላት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ለ2 ቀናት የዘለቀውን ስልጠና የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራአስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበና የተቋሙ የቢዝነስ ልማትና ማርኬቲንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አበበ የሰጡ ሲሆን ከስልጠናው ባሻገርም ከሰልጣኞች ለቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራአስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበ ከሚዲያ አካላት ጋር ተቀራርቦ በጋራ መስራት እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን አስምረው ተቋማቸውም ከሚዲያ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አንስተው ተቋሙ ከሚዲያ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራርና ተቀራርቦ መሥራት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገልፀዋል፡፡ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በተለይም ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የፋይናንስ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እየሰራ ከመሆኑም በላይ በእስካሁኑ እንቅስቃሴውም በርካታ ሴቶች ከማጀት ወደ አደባባይ ወጥተው ሰርተው እንዲለወጡ ለሌሎችም እንዲተርፉ አይነተኛ ሚና መጫወቱን አውስተዋል፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጋርም አብሮ መስራት መቻሉ ተቋሙ ለሴቶች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ውጤታማነት ያለውን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚያሳይ መሆኑም በመልዕክታቸው ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የውብዳር አክሊሉ ማኅበራቸው የሴት ጋዜጠኞችን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግና ብሎም ከተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸው ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋርም የፈጠሩት አጋርነት የዚህ አንድ አካል መሆኑን በመጥቀስ ስለ ተቋሙ የማኅበሩ አመራሮችና አባላት በቂና የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስልጠናው መዘጋጀቱን በማመላከት በቀጣይም ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሴት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተደራጅተው ሙያዊ ፍላጎትና ክህሎታቸውን ማሳደግ እንዲችሉ፣ በጾታቸው የሚደርስባቸው ተፅዕኖን ለማስቀረት፣ ከወንድ የሥራ አጋሮቻቸው ዕኩል ታይተው ያለምንም አድልኦ የሙያ ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል፣ እንዲሁም በአገራችን ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶችን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማበረታታት የተቋቋመና ከ20 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የሙያ ማኅበር ነው፡፡











Leave a Reply