የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የቅርንጫፎችና የዋናው መሥሪያ ቤት የ9 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩን ለ2 ቀናት በሐረር ወንደርላንድ ሆቴል አካሂዷል።
ለ2 ቀናት በተካሄደው የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት የግምገማ መድረክ ላይ የተቋሙ 11 ቅርንጫፎችና የዋናው መሥሪያ ቤት የሰው ሃብት ዘርፍ፣ የኦፕሬሽንና የፋይናንስ ዘርፍ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይም በሪፖርቱ አቅራቢዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በብድር ስርጭት ረገድ ለ2,821 የብድር ደንበኞች ከ635 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት ታቅዶ ለ3,005 ሰዎች ከ745 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት የተቻለ ሲሆን ይህም ተቋሙ ከዕቅድ በላይ ማከናወኑና ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡ በግምገማ መድረኩ ተመላክቷል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ለ2,389 ሥራፈጣሪዎች ከ577 ሚሊየን ብር በላይ ለማበደር ታቅዶ ለ2,568 ሥራፈጣሪዎች ከ717 ሚሊየን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መሥጠት የተቻለ ሲሆን ይህም ከዕቅድ በላይ በማከናወን ውጤታማ አፈፃፀም ማሳየት መቻሉ በመድረኩ ተንፀባርቋል።
ከብድር አመላለስ አንፃር ከ279 ሚሊየን ብር በላይ ለማስመለስ ታቅዶ ከ272 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማስመለስ የተቻለ ሲሆን ይህም የዕቅዱን 97 በመቶ በማስመለስ ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል።
በተቋሙ በብድር ደንበኞች ላይ ያለ ጠቅላላ የብድር መጠን (Total Loan Outstanding) ከ1.3 ቢሊየን ብር በላይ ማድረስ መቻሉም በመድረኩ ተገልጿል።
በሪፖርት ግምገማ መድረኩ በቁጠባ አሰባሰብና ብድርን በቁጠባ ከመሸፈን አንፃር ብሎም ውዝፍ ብድርን ከማስመለስ አንፃር አበረታች ሥራዎች እንደተሠሩ የገለፁት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ኤምአይኤስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የተቋሙ ም/ዋናስራአስፈፃሚ አቶ ፋሲል ጌታቸው ይህን አፈፃፀም ያስመዘገቡ ቅርንጫፎችን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ቅርንጫፎች ማስፋትና እርስ በእርስ መገነባባትና መማማር ላይ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የቁጠባ አሰባሰብን ማሳደግና ውዝፍ ብድር ላይ ማስመለስ ላይ ሁሉም ቅርንጫፎች በወጥነትና በዕኩል ደረጃ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የሴቶችንና ወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ተግባር በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት በመሥጠት እየተሠራ መሆኑም በም/ዋናስራአስፈፃሚው ተገልጿል።
የሴቶችንና ወጣቶችን በብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የውይይት መድረኩን የመሩት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ኤምአይኤስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የተቋሙ ም/ዋናስራአስፈፃሚ አቶ ፋሲል ጌታቸው አመላክተዋል።
የላቀ የደንበኞች አገልግሎት በመሥጠትና የደንበኞችን ዕርካታ በማሳደግ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ውጤታማነትን ማስቀጠልና ትርፋማነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ መሄድ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ይህን ያገናዘበ ሥራን በተቀናጀና በተናበበ መልኩ መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
በፋይናንስ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳዳሪና ግንባርቀደም ሆኖ ለመዝለቅ ደንበኛ ተኮር በመሆንና ለደንበኞች ቅድሚያ ትኩረት በመሥጠት ደንበኞችን በላቀ ሁኔታ ለማገልገል በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠይቅም አቶ ፋሲል አስገንዝበዋል።
የግምገማ መድረኩ የሥራ መመሪያ በመሥጠትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማመላከት ተጠናቋል።





Leave a Reply