የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም 11ኛ ቅርንጫፉን በድምቀት አስመረቀ

ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ሀሎሌ ቅርንጫፍ ሲል የሰየመውን ቅርንጫፉን የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።

ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እየደረሰና መዳረሻውንም እያሰፋ የፋይናንስ አካታችነቱንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ ይገኛል።

ተቋሙ የዚህ የፋይናንስ ተደራሽነቱ አካል የሆነውንና ወደ ደንበኞቹ የመቅረብ እንቅስቃሴው ውጤት የሆነውን ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ሀሎሌ ቅርንጫፍን ዕውን በማድረግ የምርቃት መርሃግብሩን  አካሂዷል።

የዕለቱ የክብር ዕንግዳና የድሬዳዋ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊና የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችን በማገዝና በህይወታቸው ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ መሠረት የጣለ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል። ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ የወለድ አልባ የብድርና ቁጠባ አገልግሎትንም በአግባቡ በመተግበርና ቴክኖሎጂንም በመጠቀም ረገድ አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

 የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ሀሎሌ ቅርንጫፍ ተቋሙ ተደራሽነቱን እያሰፋ የመሆኑ ማሳያ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ሙሉካ ተቋሙ ይበልጥ ዕድገቱን እንዲያፋጥንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን በላቀ ሁኔታ እንዲያገለግል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በመግለፅ በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ለተገኙ የባንክ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ለተቋሙ የድሬዳዋ አስተዳደርና የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በንግግራቸው አረጋግጠዋል።

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋናስራአስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ በበኩላቸው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና የሥራ ፈጠራ ክህሎት ኖሯቸው የፋይናንስ አቅርቦት ችግር የገጠማቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀው በከተማም በገጠርም ሐረርና ጅግጅጋን ጨምሮ ቅርንጫፎችን በመክፈት ዘመኑንም በመዋጀት ጭምር ዲጂታል ፋይናንሲንግን በመተግበር የፋይናንስ አገልግሎትን ደንበኛ ተኮር በሆነ መልኩ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ደንበኞቹን ለመቅረብና ለመድረስ ተቋማቸው ተግቶ እየሠራ መሆኑን የገለፁት አቶ ተሾመ ዛሬ የተመረቀው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ሀሎሌ ቅርንጫፍ ተቋሙ ደንበኞቹን ለመድረስ:ለኅብረተሰቡ የፋይናንስ አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ የማድረግ ሁሌም በትጋት የማገልገልና በላቀ ቁርጠኝነት የተቋሙ አመራሮች:ሠራተኞችና የድሬዳዋ አስተዳደርና የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ የማይቋረጥ የአለኝታነት ድጋፍና ክትትል ውጤት ነው ብለዋል።

በዕለቱ በዕንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣የአዋሽ ባንክና የአቢሲኒያ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ በመገኘታቸውና ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ተደራሽነቱን እያሰፋ በመሆኑ መደሰታቸውን በመግለፅ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠራሩንም  እያዘመነ መምጣቱንም አንስተዋል። የባንኮቹ ኃላፊዎች ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በመቀራረብ እየሠሩ መሆኑን በመጥቀስ ከተቋሙ ጋር ያላቸውን አጋርነትና ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስን ከትላንት እስከ ዛሬ የሚያውቁት መሥራች የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጠቅላላ ጉባኤ አባላትም ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በዚህ ደረጃ አድጎና ተለውጦ በማየታቸው ደስታቸውን ገልፀዋል።

በዕለቱ ድሬ ማይክሮ ፋይናንሰ ሀሎሌ ቅርንጫፍ ሲመረቅ ተቋሙን የሚያስተዋውቅ ሥነግጥም የቀረበ ሲሆን የምርቃት መርሃግብሩ የክብር ዕንግዶችና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች የቅርንጫፉን ቢሮና የሥራ ሂደት ጎብኝተዋል።

admin Avatar

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *