
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በሐረር ከተማ የደንበኞች ኮንፍረንስ አካሄደ
ኮንፍረንሱ ተቋሙ በሐረር የሚገኙ ምስጉን ደንበኞቹን ዕውቅና ለመሥጠትና ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካትና የአገልግሎት አሰጣጡን በይበልጥ ለማሳደግ ከደንበኞቹ ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል። የዚህው አካል የሆነውን የደንበኞች ኮንፍረንስም አካሂዷል።
በኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ደንበኞቹ ሃብቶቹ፣ ደንበኞቹ የህልውናው መሠረት መሆናቸውን በፅኑ የሚያምን ተቋም መሆኑን ጠቅሰው ደንበኛ ንጉስም ክቡርም እንደሆነም በቅጡ ይረዳል ብለዋል፡፡
ለዚህም ነው ሁሌም ለደንበኞች ዕርካታ ከፍተኛ ትኩረት በመሥጠት እየሰራ የሚገኘው ያሉት ዋና ስራአስፈፃሚው በውቢቷ፣ የታሪክና የቅርስ ማኅደሯ፣ የጭስ አልባው ኢንደስትሪ የስበት ማዕከሏ ሐረር ከተማ ከውድ ደንበኞቹ ጋር የሚያቀራርበውን፣ለቀጣይ የሰመረ የደንበኞች ግንኙነቱም መሠረት የሚጥለውን የደንበኞች ኮንፍረንስ ያዘጋጀው በማለት ተናግረዋል፡፡
ይህ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሐረር ደንበኞች ኮንፍረንስ በቀጣይ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከደንበኞቹ ጋር ለሚኖረው መስተጋብር የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን የገለፁት አቶ ተሾመ ኮንፍረንሱ ከደንበኞቹ ለቀጣይ ስራዎቹ ግብዓት የሚያገኝበት፣ የደንበኞቹን ፍላጎት በይበልጥ ለማርካት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ብርቱ ኃይል የሚሰንቅበትን ምቹ መደላድል የሚፈጥርለት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በኮንፍረንሱ ስለ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ታሪካዊ ዳራና አሁናዊ ሁኔታን ገላጭ የሆነ የመወያያ ፅሁፍ በተቋሙ ዋና ስራአስፈፃሚ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱ በኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የቁጠባ ባህላቸው እንዲያድግ መሠረት እንደሆናቸውና አካል ጉዳተኞችንም ተደራሽ በማድረግ ትርጉም ያላቸው ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል። ከወለድ ነፃ አገልግሎት ያገኘነውም በድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ነው ሲሉም የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
በቀጣይም ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል ያሏቸውንም ገንቢ ሃሳቦች ሰጥተዋል። የውይይቱ አወያዮችም ከመድረኩ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።
በኮንፍረንሱ በድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በሐረር በሚገኙት የሐረር አራተኛና የሐረር ካናል ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፎች ደንበኞች የሆኑ ምስጉን የብድርና ቁጠባ ደንበኞች እንዲሁም ከተቋሙ ጋር በጋራ እየሰሩ ያሉ አጋር አካላት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።








Leave a Reply