ከ500 በላይ የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ተዋንያን የተሳተፉበትና ላለፉት 3 ቀናት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሲካሄድ የቆየው 13ኛው ዓለም አቀፍ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን ፍፃሜውን አግኝቷል።
“ለቀጣዩ ትውልድ ማይክሮ ፋይናንስ፤ ዕድሎችን በፈጠራ፣ አካታችነት እና በማይበገሩ የፋይናንስ አገልግሎቶች መክፈት” የሚል መሪ ቃል ያነገበው ኮንፍረንሱ በኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ተደራሽነት ለማሳደግና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በቴክኖሎጂ ታግዘው ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ታልሞ የተካሄደ ነው። ኮንፍረንሱ የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍን የማዘመንና ልምድ ልውውጥ የማድረግም ተልዕኮም የያዘ ነው።
ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማህበር ከአውሮፓ ህብረት እና ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኮንፍረንሱ ከ500 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ዕንግዶች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተገኝተዋል።
የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ ከበደ እንደተናገሩት ፣ ባለፉት 28 ዓመታት የኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። በአሁኑ ወቅት በአገርአቀፍ ደረጃ 62 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ወደ ባንክነት መሸጋገራቸው ተገልጿል።
ተቋማቱ እስካሁን ድረስ ከ5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረብ ቢችሉም፣ አሁንም አገልግሎቱ ያልደረሰባቸው በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ተመላክቷል።
አቶ ተሾመ እንዳሉት የፋይናንስ ዘርፉ በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል። በተለይም የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዘርፉ መሰማራታቸው ብርቱ ውድድር እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ይህንን ውድድር ለመቋቋም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከቆየው የባህላዊ አሰራር ወጥተው ወደ ዲጂታል አማራጮች በፍጥነት መሸጋገር እንዳለባቸው አጽንኦት ተሰጥቷል።
ከመጋቢት 15-17 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደውና ለሶስት ቀናት በቆየው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ከአፍሪካ፣ ከኤዥያ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የመጡ ባለሙያዎች ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን፣ በዘርፉ የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች በርካታ የፓናል ውይይቶች ቀርበውበታል። ኮንፍረንሱ በዘርፉ አዳዲስ የቴክኖሎጂና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይም መክሯል።
በዚህ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስም ከተሳታፊዎቹ አንዱ ሲሆን በኮንፍረንሱ ከትላንት እስከ ዛሬ ያለውን ታሪካዊ ዳራውን: ያስመዘገባቸውን ውጤቶችና አሁን ያለውን ተቋማዊ ሁኔታ ብሎም ዘመኑን ከመዋጀትና አገልግሎቱን ከማዘመን ብሎም ዲጂታልና ፈጠራ የታከለበት ከማድረግ አንፃር እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ለተሳታፊዎች በተቋሙ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚና የኤምአይኤስ ዳይሬክተር አቶ ፋሲል ጌታቸው ሰፊ ገለፃ ተደርጓል።
በቀረበው ገለፃ እንዲሁም ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከኮንፍረንሱ በተጓዳኝ በተሳተፈበት ኤግዚቢሽን ተቋሙን ከማስተዋወቅና አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ከተሳታፊዎች አበረታች ግብረ መልሶችን ማግኘት ተችሏል።
ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ለኮንፍረንሱ መሳካትና ውጤታማ መሆን ላበረከተው አይነተኛ አስተዋፅኦም በኮንፍረንሱ ማሳረጊያ ዕውቅና ከፍተኛ ዕውቅና ተሰጥቶታል።
እ.ኤ.አ. በ1999 የተቋቋመው የኢትዮጵያ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት እንደ አገናኝ መድረክ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ነው።














Leave a Reply