ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የፋይናንስ አካታችነትና የፋይናንስ ተደራሽነትን ቁልፍ የትኩረት መስኩ በማድረግ በበቂ ሁኔታ የፋይናንስ ድጋፍ የማያገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ በ2017 የሂሳብ ዓመት በአዲስ አበባ በተደረገው 3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግና በማማከር አገልግሎት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ዕውቅናና ሽልማት ያገኘበት፣በተቋማዊ የሥራ አፈጻጸሙም ውጤታማ ጊዜን ያሳለፈበት ዓመት ሆኗል፡፡
የተቋሙ የ2017 የሂሳብ ዓመት ውጤታማ አፈጻጸምም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
- በ2017 የበጀት ዓመት ከዕቅዱ በላይ ለ3,871 የብድር አገልግሎት ደንበኞች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት ችሏል፡፡
- በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ለ3,259 የዘርፉ አንቀሳቃሾች 1ሚሊየን ብር የሚጠጋ የብድር ስርጭት በማድረግ የዘርፉ አንቀሳቃሾችን በፋይናንስ በመደገፍ ረገድ አይነተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
- በብድር አመላለስ ረገድ በ2017 የሂሳብ ዓመት ከ370ሚሊየን ብር በላይ ብድር ለማስመለስ ዕቅድ ይዞ የነበረው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከ380 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ተመላሽ በማድረግ ከዕቅዱ በላይ የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገብ ችሏል፡፡
- ከቁጠባ አሰባሰብ አኳያ በ2017 የሂሳብ ዓመት ተቋሙ ከ900 ሚሊየን ብር በላይ ቁጠባ ለመሰብሰብ አቅዶ ከ1ቢሊየን ብር በላይ ቁጠባ በመሰብሰብ የዕቅዱን አፈጻጸም ውጤታማ ማድረግ ችሏል፡፡
- ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በዋናነት የትኩረት ማዕከሉ ምሰሶ ከሆኑት የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴቶችና ወጣቶች የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዙ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት በ2017 የሂሳብ ዓመት ለ1943 ሴቶች ከ400 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት ችሏል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ በቅደም ተከተል በተጠቃሚዎች ብዛት 91 በመቶ በብድር ስርጭት 85 በመቶ አፈጻጸም መመዝገብ መቻሉን ያመላክታል፡፡ ይህም ተቋሙ የሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ በስፋት እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
- ወጣቶችን በተመለከተ በ2017 የሂሳብ ዓመት ወደ 3ሺ የሚጠጉ ወጣቶች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን ወደ 700 ሚሊየን ብር የብድር ስርጭት ለወጣቶቹ ማድረግ ተችሏል፡፡
- ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በ2017 የሂሳብ ዓመት መጨረሻ በተቋሙ የብድር ደንበኞች ላይ ያለው ጠቅላላ የብድር መጠን (Total Loan Outsatnding) ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡እስከ ጁን 30/2025 ያለው የተቋሙካፒታልም ከ580 ሚሊየን በላይ የደረሰ ሲሆን ይህም ተቋሙ ከጊዜ ወደጊዜ ካፒታሉን እያሳደገ መምጣቱን አመላካች ነው፡፡
- እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ድረስ ያለውን የተቋሙን የብድር አገልግሎት ደንበኞች ያየን እንደሆነ ከ10ሺ በላይ የሚሆኑ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ያሉት ሲሆን የቁጠባ ደንበኞቹ ከ90ሺ በላይ ሲሆኑ በአጠቃላይ ከ100ሺ በላይ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ደንበኞች ማፍራት ችሏል፡፡
- በአደጋ ላይ ያለውን ብድር በአስተማማኝ ሁኔታ በመቆጣጠር ውጤታማነቱንና ስኬታማነቱን ማስቀጠል የቻለው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ላለመመለስ በአደጋ ላይ ያለውን ብድር (PAR) 0.95% ማድረስ ተችሏል፡፡
- በሰኔ 30/2017 ዓ.ም ተቋሙ የተጣራ 136 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ ተቋሙ በብድር ላመጣው ገንዘብ የወለድ ወጭ ባይጨመርበት ከዚህ በላይ ብር ማትረፍ ይችል እንደነበርም ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡
ተቋሙ የአገልግሎት ተደራሽነቱን በአካባቢም በተገልጋዮችም እያሰፋ እየመጣ ሲሆን አሁን ላይ የወሽና የሶላር ኢነርጂ አገልግሎቶችን የጀመረ ሲሆን ከተቋሙ ጋር ከወሽና ከሶላር ኢነርጂ ጋር የሚሰሩ አጋር አካላት ከተቋሙ ጋር ተቀራርበው ቢሰሩ ተቋሙ ይበልጥ አገልግሎቱን ማስፋትና በርካቶችን መድረስ የሚችልበት ዕድል ይፈጥርለታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሴቶችን ዋና ማዕከሉ አድርጎ የሚሰራው ተቋሙ ከሴቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም ጋር በተያየዘ የሚሰሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጨምሮ ሌሎች አጋር አካላትም በበብዙ መመዘኛዎች ውጤታማነቱን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ከገነባው ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር ቢሰሩ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ በማሳደግ በርካታ ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል፡፡






Leave a Reply