ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በ3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ተሸላሚ ሆነ
ተቋሙ በፎረሙ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ላይ የተሳተፈው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመንግስት ከተቋቋሙ የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ተቋማት መካከል ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የላቀ የብድር፣ የቁጠባ እና የሙያ ድጋፍ በመስጠት ሶስተኛ ደረጃ በመውጣት የክሪስታል እና ሰርተፍኬት ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ እና ሌሎች ዕንግዶች በተገኙበት የተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ላይ ሲሳተፍ የቆየው ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተሸላሚ ሲሆን ይህ ፎረም የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትስስርን በማላቅ የግብርና ዕሴት ሰንሰለትን ማጎልበት፣ ዲጂታላይዜሽንና የፋይናንስ አካታችነትን ማረጋገጥ፣ ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድልን መፍጠር በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡
ፎረሙን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአፍሪካ አኀጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሪቴሪያት እና ከኤትሬድ (AeTrade Group) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በፎረሙ ሲሳተፉበት በቆየው በዚህ ፎረም ላይ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ሶስተኛ ደረጃ በመውጣቱ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበ ሽልማቱን ከክቡር አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ ተረክበዋል፡፡ ዋና ስራአስፈጻሚው ለተመዘገበው ለዚህ ደማቅ ውጤት ለድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የቦርድ ሰብሳቢ ለተከበሩ አቶ ከድር ጁሃር ለቦርድ አመራሮች፣ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም መላው ሰራተኛ ላደረገው ታላቅ ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡






Leave a Reply