የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከድሬዳዋ አስተዳደር አካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችል የኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍን አስመልክቶ ከአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ነው የተፈራረመው፡፡
በመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ የፊርማ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋናስራአስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግና የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ አይነተኛ ሚናውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነትም ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችል የኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ ለታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ተሾመ አክለውም ተቋማቸው የማኅበረሰቦችን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት የመቀነስ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆንና በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ አቶ አብዱ መሀመድ በበኩላቸው የማኅበረሰቦችን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት የመቀነስ ፕሮጀክት ለጎርፍ የተጋለጠውን የኅብረተሰብ ክፍል ከጎርፍ ስጋት በማላቀቅ የሥራ ዕድል ለማኅበረሰቡ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን በማንሳት ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር አብሮ መሥራት አቅም የሚፈጥርና ማኅበረሰቡን የሚጠቅም በመሆኑ ከተቋሙ ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈራረም ማስፈለጉን ገልፀዋል፡፡
በመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ የፊርማ ሥነስርዓት ላይ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የማኅበረሰቦችን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት የመቀነስ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አቅርቦት የሚያደርግ መሆኑና ሌላው ከአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን ጋር የተፈራረመው የኢትዮ-ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
የማኅበረሰቦችን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት የመቀነስ ፕሮጀክት ለ5 ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት ሲሆን በፕሮጀክቱ ወደ 15ሺ የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡





Leave a Reply