ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የማዕድ ማጋራት መርሐ–ግብር አካሄደ
ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ 1446ኛው የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚያሻቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ600ሺ ብር በላይ በሆነ ወጪ የማዕድ ማጋራት መርሐ- ግብር አካሂዷል።
ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ከሚሰጣቸው መደበኛ አገልግሎቶቹ በተጓዳኝ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች ግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ተቋሙ ከ120 በላይ ለሆኑ ድጋፍ ለሚያሻቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የረመዳን የፆም ወርን ምክንያት በማድረግ የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የሆኑት ክብርት ወ/ሮ ሁኩሚያ መሀመድ፣ የተከበሩ አቶ ሮቤል ጌታቸው፣የተቋሙ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ ፣የተቋሙ የሸርያ ቦርድ አባላት ሼክ ኢብራሒም ዘይኑ፣ ሼክ መሀመድ ዑመር እንዲሁም የተቋሙ የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ማዕድ አጋርቷል።
የዕለቱ የክብር ዕንግዳ፣ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሥራ አመራር ቦርድ አባልና የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሁኩሚያ መሀመድ ባስተላለፉት መልዕክት ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው የብድርና ቁጠባ አገልግሎት በተጨማሪ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን በመግለፅ በዚህ ረገድ እያበረከተ ላለው አይነተኛ አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
እርስ በእርስ መደጋገፍና መረዳዳትን የሰርክ ተግባር ማድረግና ባህል እንዲሆን መሥራት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት የሰጡት ወ/ሮ ሁኩሚያ ከተቸገሩና ድጋፍ ከሚሹ ወገኖች ጎን መሆን የተረጂነት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የድርሻውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ በበኩላቸው ተቋሙ ከሚሰጣቸው መደበኛ አገልግሎቶች በተጨማሪ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
አንዱ ለሌላው ድጋፍ በሚሰጥበትና የወንድማማችነት መንፈሳዊ ኃላፊነቱን በሚወጣበት ተካፉል የሸሪያ ህጎችን መሠረት በማድረግና ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብሩ መካሄዱን ዋና ሥራ-አስፈፃሚው ገልፀዋል።
የዕለቱ የክብር ዕንግዶችና የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ያካሄደው የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር በዋናነት በሚሰጣቸው የቁጠባና ብድር አገልግሎት የበርካቶችን ህይወት ከመለወጥና ኑሮአቸውን ከማሻሻልም አልፎ ትርፋማና ውጤታማ ከማድረግ ባሻገር ለማኅበረሰቡ ያለውን አለኝታነትና የእኔነት ስሜት ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዕለቱ የምግብ ነክ እና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቋሙ ይህን በማድረጉ የተሰማቸውን ላቅ ያለ ደስታ በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።












Leave a Reply