ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የተቋሙን ታላሚ ደንበኞች ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ አበረታች ሥራዎች እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
ተቋሙ ለ2 ቀናት ሲያካሂድ የቆየው የ2018 ሂሳብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማና የ2019 ሂሳብ ዓመት የዕቅድ ኦረንቴሽን መድረክ ተጠናቋል።
የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የ2018 ሂሳብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ስራ-አስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ አነስተኛ ገቢ ያላቸውና መጠነኛ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዋናነት የተቋሙ ታላሚ ደንበኞች መሆናቸውን በመግለፅ በዚህም በ2018 የሂሳብ ዓመት በተለይም ለቡድን ብድር ልዩ ትኩረት በመሥጠት 105 ሚሊየን ብር ለ1,658 ደንበኞች ብድር መሠራጨቱን ተናግረዋል።
ዋና ስራ-አስፈፃሚው የተቋሙ በደንበኞች ዕጅ ያለ ጠቅላላ የብድር መጠን /ቶታል ሉዋን አውትስታንዲንግ/ ከ1.8 ቢሊየን ብር በላይ እና የተቋሙ ካፒታልም ከ750 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱን አመላክተው የተቋሙ የተጣራ ቁጠባን ከ 1.3 ቢሊየን ብር በላይ ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል። በበጀት ዓመቱ ለ3,765 ሰዎች ከ960ሚሊየን ብር በላይ በማሰራጨት በሰው 90 በመቶ በብር 88 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገቡንም አንስተዋል ላለመመለስ በአደጋ ላይ ያለ ብድርን/ፓር/ 0.65 ማድረስ መቻሉንም በማከል።
በ2019 የሂሳብ ዓመት ለ4,756 የብድር ደንበኞች ከ1.2 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለማሰራጨት እንዲሁም በቁጠባ አሰባሰብ ረገድ በሂሳብ ዓመቱ ከ2.7 ቢሊየን ብር በላይ ቁጠባ ለማሰባሰብ መታቀዱን ዋናስራአስፈፃሚው አብራርተዋል።
በቀጣይ የገጠር እና የሴቶች ብድር ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራአስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበ አሳስበዋል ።
በመድረኩ የተቋሙ ቅርንጫፎችም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርታቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎበት የሥራ መመሪያ የተላለፈ ሲሆን የተቋሙ የ2019 ሂሳብ ዓመት ዕቅድና የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችም ቀርበዋል።








Leave a Reply