የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በ2017 በጀት ዓመት ወደ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ለማሰራጨት መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በ2017 በጀት ዓመት ወደ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ለማሰራጨት መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡

በዚህም ከሶስት ሺ አምስት መቶ በላይ የብድር ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሥራ አመራር ቦርድ በአዲስ አበባ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መሰብሰቢያ አዳራሽ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ባደረገው ስብሰባ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን ገምግሞ አጽድቋል፡፡

የሥራ አመራር ቦርዱን ስብሰባ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ከድር ጁኸር የመሩት ሲሆን ፣ በሥራ አመራር ቦርዱ ስብሰባ ላይ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡት የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ አበበ የተቋሙ ካፒታል ከ430 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱን ፣ በበጀት ዓመቱም ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ማትረፉንና ጠቅላላ ሀብቱም ከ1.3 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን ገልፀዋል፡፡ ተቋሙ በብድር ስርጭት ረገድ አፈጻጸሙ ከ100 ፐርሰንት በላይ መሆኑንና  በተበዳሪዎች ብዛትም ከ89 በመቶ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር እንደገለጹት ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በበጀት ዓመቱ ያከናወነው ተግባር አመርቂ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በአስተዳደሩ በሚከናወኑ የልማት እና እድገት ስራዎች ላይ ተቋሙ ጉልህ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የሥራ አመራር ቦርድ በ2017 በጀት ዓመት 1ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ለማሰራጨት የታቀደውን ዕቅድ ገምግሞ ያፀደቀ ሲሆን በዚህ ብድር ስርጭትም ከ3500 በላይ የሆኑ ተበዳሪዎች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቁጠባ አሰባሰብ ረገድ የሥራ አመራር ቦርዱ ከ958 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ የታቀደውን ዕቅድ ገምግሞ ያፀደቀ ሲሆን የተቋሙ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ተወያይቶና ገምግሞ ዕቅዱን አፅድቋል፡፡ በተጨማሪም የሥራ አመራር ቦርዱ የተቋሙን የአሰራር ሥርዓት የሚያሻሽሉና አገልግሎት አሰጣጡን የሚያቀላጥፉ ልዩ ልዩ የአሰራር መመሪያዎችን አፅድቋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የቦርድ ሰብሳቢ አስተዳደሩ ተቋሙን ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑንና በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ክቡር አቶ ከድር ጁኸር የሥራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን የሥራ አመራር ቦርዱም ተቋሙን በሀብት አሰባሰብ ለመደገፍ የሚያስችል አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡

admin Avatar

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *